መግቢያ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች በርካታ አዎንታዊ ለውጦችን አስመዝግባለች። እነዚህን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች አስጠብቆ ለማስፋት፣ ስህተቶችን ለማረም እንዲሁም የዛሬውንና የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ወቅቱ ለሚጠይቀው ትግል በሚመጥን መልኩ ለመደራጀት አምነው የፈፀሙትን ውህደት መነሻ በማድረግ ይህ የ”ብልጽግና ፓርቲ” ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።
የብልጽግና ፓርቲ ዓላማና መለያ ዕሴቶች
ፓርቲያችን ሀገራችንን የሚመለከትበት የዕይታ ማዕቀፍ በጥቅሉ የነበረውን ጠንካራ መሰረት በማስጠበቅ እና ውስንነቶችን በማረም ሁለንተናዊ የብልጽግና ምዕራፍ መክፈት የሚል ነው። ይህን የዕይታ ማዕቀፍ በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በተለያዩ ቡድኖች፣ መደቦች፣ ማንነቶች፣ ወዘተ የሚስተዋሉ ዋልታ- ረገጥ አስተሳሰቦች ሚዛን ጠብቀው እንዲሄዱ ያደርጋል።
የፖለቲካ ፕሮግራም
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው፣ የብሔር ማንነትን እና የሀገራዊ አንድነትን ሚዛን የጠበቀ ሀገረ-መንግስት መገንባት ነው። ከጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ አንፃር ፓርቲያችን ህዝብ ከቀጥተኛ የህልውና አደጋ ተጠብቆ የልማት፣ የእኩልነት እና የነፃነት ፍላጎቶቹ እንዲሟላለት የሚያስችል ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃትን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ ተቋማዊ አደረጃጀት መገንባት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል።
የኢኮኖሚ ፕሮግራም
የብልጽግና ፓርቲ በኢኮኖሚ ፕሮግራሙ የህዝባችን ሰፊ ክፍል የሆነውን አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ወጣት፣ ሴቶች እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማ ነዋሪዎች ማዕከል ያደረገ አካታች የኢኮኖሚ ስርዓት በመገንባት የህዝባችንን የጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ዓላማ ይኖረዋል።
ማህበራዊ ፕሮግራም
ሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት መነሻዋ ዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ ሁለንተናዊ ማህበራዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዳይ የፓርቲያችን ማህበራዊ ፕሮግራም አንድ ዋና ትኩረት ይሆናል። በመሆኑም የማህበራዊ ልማት ስራዎቻችን የዕድገትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መንትያ ግቦችን የማሳካት ጉዳይ ይሆናል።
የውጭ ግንኙነት ፕሮግራም
ፓርቲያችን የውጭ ጉዳይን ከሀገር ውስጥ ጉዳይ የተነጠለ አድርጎ አይመለከትም። ይልቁንም የሀገር ውስጥ ጉዳያችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች ነፀብራቅ ሆኖ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ያልዘነጋ ነው።